በወሎ ዩኒቨርሲቲ የባህል ሙዚቃ አውደ ጥናት ተካሄደ።
  February 17, 2019    News

ሙዚቃ በቋንቋ ሳይገደብ የአለምን ህዝብ በማህበራዊ ትስስር በማቆራኘት በህዝቦች መካከል ያለውን ውህደት ይበልጥ እያጠነከረ ከመምጣቱም ባሻገር ጭስ አልባ የኢኮኖሚ ሴክተር በመሆን የሀገር የኢኮኖሚ ምንጭ ሁኖ ያገለግላል። በሀገራችን ያለው የሙዚቃ ታሪክ ወደ ኋላ ሲዳሰስ ከቅኝትና ከሌሎች መሰረታዊ የሙዚቃ ባህሪያት አንጻር በመነሻነት ወሎ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ይገኛል። በዚህ የወሎ ህዝብ ሀብት በሆነው ሙዚቃ ላይ ጥናቶችን በማካሄድ የወሎን ባህላዊ ሙዚቃ በማሳደግ ህዝቡ የባህሉና የትውፊቱ ተጠቃሚ እንድሆን የወሎ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማእከሉን በኪነ ጥበብና ሙዚቃ ላይ አድርጎ መስራት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። ዩኒቨርሲቲው ይህንን ተልእኮውን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ ከጥር 4-5/11 ዓ ም "የባህል ሙዚቃ አውደ ጥናት" አካሄዷል። በዚህም አውደ ጥናት የደሴ ከተማ፥ የደቡብ ወሎና የከሚሴ ብሄረሰብ ዞን የባህልና ቱሪዝም ባለሞያዎች ተሳታፊ ሲሆን ከወሎና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ት/ቤት በመጡ መምህራን ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል። ይህንን የባህል ሙዚቃ አውደ ጥናት በይፋ የከፈቱት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን የባህል ሙዚቃና የኪነ ጥበብ አውድማ በሆነው ወሎ ያለውን ተዝቆ የማያልቅ ሀብት በማሳደግ የህዝቡን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል። በዚሁ አውደ ጥናት ቁልፍ ንግግር ያደረጉት በአድስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት መምህር የሆኑት ዶ/ር እዝራ አባተ በወሎ አካባቢ ያለውን ተዝቆ የማያልቅ የኪነ ጥበብ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ወሎ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ት/ቤትና የባህልና ኪነ ጥበብ ዳይሬክተር ጽ/ቤት በመክፈት እንድህ አይነት የባህል ሙዚቃ አውደ ጥናት እንድካሄድ ማድረጉ እስካሁን በጥናት ያልታዩና ያልተፈተሹ የሙዚቃ ስልተ ምት፥ ቅኝትና ሌሎች ተጨማሪያ ባህሪያቶችን እንድፈተሹ በር ይከፍታል ሲሉ ተናግረዋል። ታዋቂው የሙዚቃ ባለሞያ ሰርጸፍሬ ስብሀት በወሎ ማህበረሰብ ውስጥ ገና ያልታዩ እምቅ የባህል ሙዚቃ ሀብቶችን በጥናት ለመዳሰስ በዩኒቨርሲቲው የተጀመረው እንቅስቃሴ ይበል የሚያስብል ህብረተሰቡን የባህሉ የታሪኩና የሀብቱ ተጠቃሚ በማድረግ ማህበራዊ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው ብለዋል። በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው የባህልና ኪነ ጥበብ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አጸደ ተፈራ ዩኒቨርሲቲው ያካሄደው የባህል ሙዚቃ አውደ ጥናት ቀጣይነት ያለው የአካባቢውን ማህበረሰብ እድገት ሊያመጣ በሚያስችል መልኩ ተቋሙ በረጅም ጊዜ "የባህል ኢንዱስትሪው" የት መድረስ እንዳለበት አቅዶ እየሰራ ነው ብለዋል።