ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን ለማነቃቃትና አዳዲስ ስራዎች ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት አካሄደ።
  December 01, 2018    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን ለማነቃቃትና አዳዲስ ስራዎች ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት አካሄደ። በየአመቱ የሚከበረውን አለም አቀፍ የተሳካላቸው የስራ ፈጠሪዎች ሳምንት ምክንያት በማድረግ የወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ከተማ በደቡብ ወሎና በከሚሴ አስተዳደር ዞን የራሳቸውን ስራ ከፈጠሩ ኢንተርፕራይዞችና ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ከመጡ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል። ይህንን ቀን ምክንያት በማድረግ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ጀምረው የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ በማሳየት የአሰራርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል የተሳካላቸው ስራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ የሚያስችሉ ጥናቶች ቀርበዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለኢንተርፕራይዞችና ስራ አጥ ወጣቶች ስኬታማነትና ወደ ስራ ሊያስገቡ የሚችሉ ስልጠናዎችን መስጠት ነው ያሉት የቢዝነስ ልማትና ስራ ፈጠራ ዳይሬክተር ዶ/ር ካሰኝ ዳምጤ በደቡብ ወሎ በደሴ ከተማና በከሚሴ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ የስራ አጦች ቁጥር በመኖሩ ዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕራይዞችን ለማነቃቃትና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አካሄዷል ሲሉ ገልጸዋል። አያይዘውም ዳይሬክተሩም በአካባቢያችን ያለውን ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ወደ ስራ ለማስገባት ዩኒቨርሲቲው ግንዛቤ የመፍጠሩን ስራ ከሰራ ከተማ አስተዳደሩና ዞኑ ለወጣቶች ምቹ የስራ ሁኔታዎችን በመፍጠር ወጣቶችን ወደ ስራ ለማሰማራት የሚያስችል ተመጋጋቢነት ያለው ተግባር እንዲኖር በቅንጂት እየሰራን ነው ብለዋል። በውይይቱ ከአማራ ክልል ስራ ፈጠራ ማእከል ከደሴ ከተማ ከደቡብ ወሎና ከከሚሴ አስተዳደር ዞን የሚመለከታቸው የመንግስት አካሎች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማትና የዘርፉ ባለሞያዎች ተሳትፈዋል። ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ስራ አጥ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ምቹ ሁኔታ በማየት ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችል ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን በማሳወቅ ውይይቱ ተጠናቋል።