በምስራቅ አማራ የተሳለጠ የንግድ ልውውጥ በአምራቹና በአቅራቢው የንግዱ ማህበረሰብ መካከል ለመፍጠር የሚያስችል የአቻ ላቻ ውይይት ተካሄደ።
  December 01, 2018    News

በምስራቅ አማራ የተሳለጠ የንግድ ልውውጥ በአምራቹና በአቅራቢው የንግዱ ማህበረሰብ መካከል ለመፍጠር የሚያስችል የአቻ ላቻ ውይይት ተካሄደ። በምስራቅ አማራ በአምራቾችና አቅራቢዎች የንግድ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የንግድ የልውውጥ ተግዳሮቶች በማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቹ በምርምርና ጥናት ለመፍታት የወሎ ዩኒቨርሲቲ በአጋርነት ይሰራል። በኢትዮጵያ በክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በአምራቾች፣ በላኪዎች፣ በአቅራቢዎችና በአስመጭዎች መካከል የቢዝነስ የአቻ ለአቻ የንግድ ግንኙነት በኢንዱስትሪዋ መንደር ኮምቦልቻ አካሄዷል። በምስራቅ አማራ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ምእራፍ ለማሸጋገር በኢንዱስትሪዋ ኮሪደር ኮምቦልቻ በንግዱ ማህበረሰብ የተካሄደው የቢዝነስ የአቻ ለአቻ ግንኙነት በቀጠናው ያጋጠሟቸውን የማምረትና የአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን ለመፍታት ፊት ለፊት ከመነጋገር ባሻገር በሻጭና ገዥ መከከል ትውውቆችን ፈጥሯል። በዚህ የነጋደዎች የአቻ ለአቻ ውይይት ላይ የተገኙት የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ኢንጂነር ከማል መሀመድ ዘይን እስካሁን በሀገር ደረጃ ከሌሎች የውጭ ሀገር የንግድ ማህበረሰብ ጋር የነበረው ግንኙነት ወደ ታች ወርዶ በከተማችን መካሄዱ በከተማዋ ያለውን ኢንቨስትመት፣ ልማትና የንግድ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ለባለሀብቶች የልማት ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን ለማስተካከል ተግቶ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል። በንግዱ ማህበረሰብ መካከል የተጀመረው የአቻ ለአቻ ውይይት አምራቾችንና አቅራቢዎችን ፊት ለፊት በመገናኘት በምናመርታቸውና በምንፈልጋቸው ምርቶች ላይ ተወያይተን የንግድ ትስስር እንድንፈጥር በር ከፍቶልናል ሲሉ አስተያየት የሰጡት የንግዱ ማህበረሰብ በከተማ አስተዳደሩ ያለው የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትና የጥራት ደረጃ ተጠሪ መስሪያ ቤቶች ከከተማው ውጭ መሆኑ አማራቹን እያስመረሩ ያሉ በመሆናቸው የመንግስትን ትኩርት ይሻሉ ብለዋል። በንግዱ ማህበረሰብ የቢዝነስ የአቻ ለአቻ ግንኙነት ከበርካታ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንጻር በኮምቦልቻ እንድካሄድ ተደርጓል ያሉት የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ምክትል ጸሀፊ አቶ አህመድ ሀሰን ለንግዱ ማህበረሰብ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በንግድና ዘርፍ ማህበራት በኩል ለመፍታት የአቻ ለአቻ ውይይቱ የሚመለከታቻውን የመንግስት አካላት በማካተት ጭምር መካሄዱ በአምራቾችና አቅራቢዎች የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ያግዛል ሲሉ አብራርተዋል። በቀጣይም የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ከዞን እስከ ወረዳ ያለውን ተጠረ ተቋም በማጠናከር የንግዱ ማህበረሰብ ተግዳሮቶች በየደረጃው የሚፈቱበትን ስትራቴጂ ለማስቀመጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አቶ አህመድ ተናግረዋል።