በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ መማር ማስተማር በ2011 የትምህርት ዘመን ለማስቀጠል የሀይማኖት አባቶች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ።
  December 14, 2018    News

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ መማር ማስተማር በ2011 የትምህርት ዘመን ለማስቀጠል የሀይማኖት አባቶች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ።በ2011 ዓ ም የተሳለጠ የስልጠና ፕሮግራም ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ከነባር ተማሪዎች ጋር በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታና በ2011 የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት ያደረገው የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላም አምባሳደርነቱን ለማስቀጠል የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሷል።በዚህ ውይይት የተገኙት የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ የሀይማኖት አባቶች በተማሪዎች መካከል ያለውን አንድነት መቻቻልና አብሮነት እንድቀጥል የአባትነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከዩኒቨርሲቲው ጋር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።ሰላም፣ይቅርታ፣ፍቅር፣መደመርና አንድነት የሁሉም ሀይማኖቶች መሰረቶች ናቸው ያሉት በደቡብ ወሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተወካይ አባ ኪዳንማሪያም አባቶቻችን በዘር፣ በሀይማኖትና በቋንቋ ሳይከፋፈሉ አንድ በመሆናቸው መካከለኛውን ምስራቅ ጭምር ሲያስተዳድሩ እንደነበር በመግለጽ በተቋሙ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል በሰላም እሴት ግንባታ ከዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጂት የእምነት ተቋሙ እንደሚሰራ ገልጸዋል።ወሎ የብዝሀነትና የአብሮነት ተምሳሌት በመሆኑ ተማሪዎች ቋንቋ፣ ዘርና ሀይማኖት ሳይከፋፍላቸው የኢትዮጵያን ብሎም የወሎን በፍቅር አብሮ የመኖር እሴት ለማስቀጠል ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በቅርበት እንሰራለን ያሉት የደሴ ከተማ የእስልምና እምነት ተወካይ ሀጂማህሙድ አደም ሁሉም ለሰላም ዘብ በመቆም ተማሪውም ለትምህርቱ ሌላውም ለተሰለፈበት ዓላማ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።የኢትዮጵያ መካነ እየሱስና የካቶሊክ የእምነት ተወካዮችም በበኩላቸው በእምነት ተቋማቸው በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ መማር ማስተማር ለማስቀጠል በተቋሙ ውስጥና ከተቋሙ ውጭ ጭምር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።በሀገራችን ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡ አስገራሚ ለውጦችን ተከትሎ አልፎ አልፎ የተከሰቱ ተግዳሮቶች የሰላም እጦት አስከትለዋል ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በለውጥ ሂደት ውስጥ መንገራገጭ የማይቀር ማህበራዊ ክስተት በመሆኑ ተማሪዎች በማህበራዊ ሜድያም ሆነ በተለያዩ የመልእክት ማስተላለፊያ መንገዶች ከሚሰሟቸው አፍራሽ መልእክቶች ራሳቸውን በማራቅ ለሰላም ዘብ እንድቆሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋልአያይዘውም ፕሬዚዳንቱ 2011 ዓ ምን በሰላም፣ በይቅርታ፣ በፍቅር፣ በመደመርና በአንድነት ቀኖች ከፋፍለን የተቀበልን በመሆናችን እሴቶቹ የተቋማችን መለያ ሁነው እንድቀጥሉ ተማሪዎች በመካከላችሁ ችግሮች እንኳን ቢከሰቱ በአባቶቻችን የግጭት አፈታት ዘዴዎች በመፍታት የሰላም አምባሳደርነታችሁ እንድታስቀጥሉ ዩኒቨርሲቲው ከጎናችሁ ነው ሲሉ መልእክታቸውን ገልጸዋል።ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ያለውን ሰላማዊ መማር ማስተማር ከፕሬዚዳንቱና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ለማስቀጠል ያላቸውን አጋርነት በአንድ ድምጽ ገልጸዋል ሲል የተቋሙ የውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት ዘግቧል።Image may contain: 1 person, standing